ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ወደ ዲያጎ ጋርሲያ ሚሳዔሎች መተኮሳቸውን ተከትሎ ዩኬ 'ግድ የለሽ' ያለቻቸውን "የኢራን ማስጠንቀቂያዎች' አወገዘች
የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገራቸው "ለግድ የለሽ የኢራን ማስፈራሪያዎች" የመከላከያ ድጋፍ መስጠቷን እንደምትቀጥል ገልጸው፤ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ ግጭት እንደማትገባ ግን አጥብቀው ተናግረዋል።
ዪቬት ኩፐር ይህንን የተናገሩት ቴህራን በቻጎስ ደሴቶች በሚገኘውን የአሜሪካ-ዩኬ ወታደራዊ ጥምር የጦር ሠፈርን ዒላማ ማድረጓ ከታወቀ በኋላ ነበር። ሁለት የባለስቲክ ሚሳዔሎች በዲያጎ ጋርሲያ ደሴት ላይ እንደተኮሱም ሪፖርቶች አክለው ገልጸዋል።
የዩኬን ጥቅም መደገፍ በባለስቲክ ሚሳዔል ስጋቶች ላይ የመከላከል እርምጃ መውሰድን ያካትታል ሲሉም አክለዋል።
ዩኬ "ኢራን ለዓለም አቀፍ መርከቦች የደቀነችውን ስጋት እንዲሁም ለባሕረ ሰላጤ አጋሮቻችን ያላት ስጋት" እውቅና ሰጥታለች ያሉት ኩፐር፤ አገራቸው ግጭቱ በፍጥነት እንዲቆም እንደምትፈልግ በድጋሚ ገልጸዋል።
ዎል ስትሪት ጆርናል እና ሲኤንኤን ስማቸው ያልተጠቀሰ የአሜሪካ ባለሥልጣናትን በመጥቀስ በዲያጎ ጋርሲያ ላይ የባለስቲክ ሚሳዔሎች ቢተኮሱም ዒላማቸውን እንዳልመቱ ዘግበዋል።
ከተተኮሱት ሚሳኤሎች አንዱ በበረራ ላይ መውደቁን እና ሌላኛው ደግሞ በአሜሪካ የጦር መርከብ መክሸፉ ተዘግቧል። ቢቢሲ ሪፖርቶቹ ትክክለኛ መሆናቸውን ተረድቷል። ኢራን 2 ሺህ 350 ማይል ያህል ርቀት ላይ የሚገኘውን ዲያጎ ጋርሲያን ለመድረስ የሚችሉ ሚሳዔሎችን ስለመታጠቋ ጥርጣሬ አለ።
ኢራን ሚሳዔሎቹን የተተኮሰችው ከሐሙስ ምሽት እስከ አርብ ጠዋት ባለው ጊዜ እንደሆነ ቢቢሲ ተረድቷል።
መጀመርያ ላይ የወጣው መረጃ ውስን የነበረ ሲሆን በወቅቱ ሚኒስትሮች ስለ ጦርነቱ ለመወያየት በለንደን ተሰባስበው ነበር።
ዩኬ አሜሪካ የእንግሊዝ ወታደራዊ ሰፈሮችን ተጠቅማ ኢራን በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በኩል የሚያልፉ መርከቦችን ዒላማ ለማድረግ የምትወስደውን ጥቃት ለማስቆም ተስማምታለች።
የአሜሪካ ጦር ስለ ጉዳዩ አስተያየት ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ቅዳሜ ዕለት ባደረጉት ቃለ ምልልስ የዩኬን አቋም በድጋሚ አረጋግጠዋል።
"ጠቅላይ ሚኒስትሩ እነዚህን ግድየለሽ የኢራን ማስፈራሪያዎችን ለመከላከል የመከላከል ድጋፍ እንደምንሰጥ ግልፅ አድርገው አስቀምጠዋል። ነገር ግን በጥቃት እርምጃ ውስጥ አሁንም ወደፊትም አንሳተፍም" ብለዋል።
"ወደ ሰፊ ግጭት አንገባም ምክንያቱም በዩኬ ብሔራዊ ጥቅም ላይ በተቻለ ፍጥነት መፍትሄ ማየት አለብን ብለን እናስባለን" ሲሉም አክለዋል።
በዲያጎ ጋርሲያ የሚገኘው የአየር ኃይል ሠፈር ስትራቴጂካዊ በሆነ ቦታ ላይ የሚገኝ ሲሆን የረዥም ርቀት ቦምብ ጣዮችን ማስተናገድ የሚችል ሲሆን ለዓመታት በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚደረጉ ዘመቻዎች መነሻ አገልግሏል።
የዩኬ መንግሥት የአየር ሠፈሩን የፈቀደው በክልሉ ውስጥ የዩኬን ፍላጎቶች እና አጋሮችን ዒላማ የሚያደርጉ ጥቃቶችን ለማስቆም ብቻ እንዲውል በሚል ነው።
መንግሥት አርብ ዕለት አሜሪካ የሆርሙዝን ወሽመጥ ዒላማ ለማድረግ ኢራን የምትጠቀምባቸውን ይዞታዎች ለማጥቃት የዩኬ ጦር ሠፈሮችን እንድትጠቀም ለመፍቀድ መስማማቱን አስታውቋል።
ቅዳሜ ዕለት ጠቅላይ ሚንስተር ሰር ኪር ስታርመር ከቆጵሮስ ፕሬዝዳንት ጋር በተነጋገሩበት ወቅት ራፍ አክሮቲሪ አሜሪካ የኢራን የሚሳዔል ጣቢያዎች ዒላማ ለማድረግ ከሚጠቀምባቸው ሠፈሮች አንዱ እንደማይሆን በድጋሚ ተናግረዋል።
ቴህራን በቆጵሮስ በሚገኘው ወታደራዊ ጣቢያ ላይ በርካታ ሰው አልባ ድሮኖችን አስወነጭፋ አንዱ በመንደርደሪያው ላይ "አነስተኛ" ጉዳት ማስከተሉ ይታወሳል።