ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዩቲዩብ እና ሜታ ለታዳጊዎች ሱስ አስያዥ ናቸው በሚል ክስ ጥፋተኛ ተብለው ተፈረደባቸው
የሎስ አንጀለስ ዳኞች በልጅነቷ የማኅበራዊ ሚዲያ ሱሰኛ በመሆኗ ምክንያት ሜታ እና ዩቲዩብ ላይ ክስ ለመሰረተችው ግለሰብ ከፍተኛ ካሳ እንዲከፈላት ወሰኑ።
ካሌይ በመባል የምትታወቀው ክሱን የመሠረተችው ግለሰብ፣ ለደረሰባት ጉዳት 6 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲከፈላት ተወስኗል።
ዳኞቹ የኢንስታግራም እና ፌስቡክ ባለቤት የሆነው ሜታ እና የዩቲዩብ ባለቤት ጎግል ሆን ብለው በ20ዎቹ የሚገኙ ወጣቶችን የአእምሮ ጤና የሚጎዳ ሱስ አስያዥ ማኅበራዊ ሚዲያ ሰርተዋል ብለዋል።
ይህ ውሳኔ ወደ አሜሪካ ፍርድ ቤቶች እያመሩ ለሚገኙ ተመሳሳይ ክሶች መንገድ ጠራጊ ነው ተብሏል።
ሜታ እና ጎግል በየግላቸው በውሳኔው እንደማይስማሙ የገለፁ ሲሆን፣ ይግባኝ እንደሚጠይቁም ተናግረዋል።
ሜታ "የታዳጊዎች አእምሮ ጤና በመሠረታዊነት ውስብስብ ነው፤ እናም ከአንድ ነጠላ መተግበሪያ ጋር ብቻ አይገናኝም፤ እያንዳንዱ ክስ የተለያየ በመሆኑ ራሳችንን መከላከላችንን እንቀትላለን፤ እንዲሁም ታዳጊዎችን በኦንላየን ላይ በመከላከል ረገድ ባለን ስም እንተማመላለን"
የጎግል ቃል አቀባይ በበኩላቸው "ይህ ክስ ዩቲዩብን አልተረዳም፤ ኃላፊነት የሚሰማው የስትሪሚንግ መድረክ እንጂ የማኅበራዊ ሚዲያ አይደለም" ብለዋል።
ዳኞቹ ካሌይ ለደረሰባት ጉዳት 3 ሚሊዮን ዶላር ካሳ እንዲሁም ተጨማሪ 3 ሚሊዮን ዶላር ደግሞ የቅጣት ገንዘብ እንዲከፈላት ወስነዋል።
ዳኞቹ ለውሳኔ ያበቃቸውን ምክንያት ሲያስረዱ ሜታ እና ጉግል ገጾቻቸው ላይ "ሆን ብለው በመጫን ወይም በማጭበርበር እርምጃ ወስደዋል" ብለዋል።
ሜታ ካሌይ ላይ የደረሰውን ጉዳት 70 በመቶ የሚወስድ ሲሆን ጉግል ደግሞ 30 በመቶ ያህሉን ይጋራል።
በካሌይ ክስ ላይ ያልተካተቱ እና በማኅበራዊ ሚዲያዎቹ ጉዳት ደርሶብናል ያሉ የሌሎች ልጆች ወላጆች ረቡዕ ዕለት ውሳኔው ሲሰጥ ከችሎት ውጪ ተሰባስበው ታይተዋል።
ችሎቱ ጉዳዩን ለአምስት ሳምንታትን ያህል ሲመለከት ቆይቷል። የችሎቱ ውሳኔ ሲሰማ ወላጆች ሲተቃቀፉ እና ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።
የሎስ አንጀለሱ ውሳኔ የመጣው በኒው ሜክሲኮ የሚገኝ ፍርድ ቤት ሜታ ሕጻናትን ለአደጋ አጋልጧል ሲል ጥፋተኝነት ውሳኔ ባስተላለፈ ማግሥት ነው።
ፍርድ ቤቱ ሜታ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ ለልጆች ምን ያህል ደኅንነታቸው የተጠበቀ መሆኑን በተመለከተ አሳሳች መረጃ ሰጥቷል በሚል 375 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ጥሎበታል።
የፌስ ቡክ፣ የኢንስታግራም እና የዋትስአፕ ባለቤት የሆነው ሜታ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮቹ ሕጻናትን ለወሲባዊ ይዝቶች እንዲሁም ለወሲብ አዳኞች ተጋላጭ በማድረግ ተጠያቂ መሆኑን ዳኞች አረጋግጠዋል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ አውስትራሊያ ያሉ አገራት ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊዎች ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚያደርጉ ሕጎችን እያወጡ እና እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው።
ዩናይትድ ኪንግደም እንዲሁ ዕድሜያቸው ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናትን ከማኅበራዊ ሚደያ ማገድ ያለውን ተጽዕኖ ለመገምገም የሙከራ ፕሮግራም እያካሄደች ነው።
በየካቲት ወር ዳኞች ፊት የቀረበው የሜታ ሊቀመንበር እና ስራ አስፈጻሚ ማርክ ዙከርበርግ ኩባንያው ዕድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ሕጻናት በየትኛውም ማኅበራዊ ሚዲያን እንዳይጠቀሙ የሚያደርግ ረዥም ጊዜ የቆየ ፖሊሲ እንዳለው ገልጿል።
ሜታ ታዳጊ ሕጻናት ማኅበራዊ ሚዲያዎቹን ይጠቀሙ እንደነበር እንደሚያውቅ የሚያሳይ የኩባንያውን ሰነዶች እና ጥናቶች ሲቀርብለት ዙከርበርግ ዕድሜያቸው ከ13 ዓመት በታች የሆኑ ታደጊዎችን ለመለየት ፈጣን መንገድ ቢኖር "ሁሌም እንደሚመኝ" ተናግሯል።
በዚህ ክስ ላይ ተካትተው የነበሩት ስናፕቻት እና ቲክቶክ ከችሎቱ በፊት መጠኑ ያልተገለጸ ገንዘብ ለመክፈል ከካሌይ ጋር መስማማታቸው ተገልጿል።
የካሌይ ጠበቆች ሜታ እና ዩቲዩብ "ሱስ አስያዥ" ማሽን ገንብተዋል ሲሉ ተከራክረው፣ ሕጻናት እነዚህን ሚዲያዎች እንዳይጠቀሙ የማድረግ ኃላፊነታቸውን አልተወጡም ብለዋል።
ካሌይ ኢንስታግራም መጠቀም የጀመረችው የዘጠኝ ዓመት ልጅ እያለች መሆኑን ገልጻ፣ ዩቲዩብ ደግሞ ከስድስት ዓመቷ ጀምሮ ብትጠቀምም ማንም በዕድሜዋ ምክንያት ገደብ እንዳልጣለባት ተናግራለች።
ካሌይ ለችሎቱ ስታስረዳ "ጊዜዬን በሙሉ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ስለማጠፋ ከቤተሰብ ጋር መገናኘቴን አቆምኩ" ብላለች።
ካሌይ የጭንቀት እና የድብርት ስሜት ሲጀምራት የ10 ዓመት ልጅ እንደነበረች ገልጻ በዚህም የተነሳ በገጠማት የጤና መታወክ ከዓመታት በኋላ ባለሙያ ማየት ጀምራለች።
በማኅበራዊ ሚዲያዎቹ የተነሳ ስለ ተክለ ሰውነቷ መጨነቅ እንደ ጀመረች እና መልኳን የሚቀይሩ አፍንጫዋን ትንሽ ዓይኗን ጎላ ጎላ የሚያደርጉ የኢንስታግራም ፊልተርስን መጠቀም የጀመረችው በልጅነቷ እንደሆነ አብራርታለች።