ቻይና የኢራን መርከብ በአሜሪካ መያዙ “እንዳሳሰባት” ገለጸች
የኢራንን ባንዲራ የሚያውለበልበው ቱስካ የጭነት መርከብ በአሜሪካ መያዙን ተከትሎ በሁለቱ አገራት መካከል የሰላም ንግግር እንዲጀመር የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ጥሪ አቀረቡ።
ቃል አቀባዩ ጉኦ ጂያኩን ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የአሜሪካ ኃይሎች መርከቡን “በኃይል መጥለፋቸው” ቻይናን “እንዳሳሰባት” መናገራቸውን የዜና ወኪሉ ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ሌላኛው የዜና ወኪል አሶሺዬትድ ፕሬስ ያወጣው ዘገባ ደግሞ ቃል አቀባዩ፤ “ሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች ኃላፊነት የተሞላበት አቋም እንደሚይዙ፣ በተኩስ አቁም ስምምነቱን እንደሚያገዙ፣ ውጥረቶችን ከመጨመር ወይም ቅራኔዎችን ከማባባስ እንደሚቆጠቡ ተስፋ እናደርጋለን” ማለታቸውን ያመለክታል።
“የሆርሙዝ ወሽመጥ ዓለም አቀፍ የውሃ መስመር ነው፤ ያለ ምንም እንቅፋት ክፍት ሆኖ መቆየቱንም ማረጋገጥ የቀጠናው አገራት እና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የጋራ ጥቅም ነው” ሲሉም አክለዋል።
የቻይን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም አሜሪካ ወደ ኢራን ወደቦች የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ የጣለችውን እገዳ “ኃላፊነት የጎደለው እና አደገኛ” ሲል ጠርቶ ነበር።
ከኢራን ለውጭ ገበያ ከምታቀርበው የነዳጅ ምርት ውስጥ 90 በመቶ ገደማውን የምትገዛው ቻይና እንደሆነች ይገመታል። ተንታኞች፤ አሜሪካ ወደ ወደቦቹ የሚደረግ ጉዞ ላይ እገዳ የጣለችው ቻይና ኢራን ላይ ጫና እንድታሳድር ለማድረግ ሊሆን ይችላል የሚል አስተያየት እየሰጡ ነው።