ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዓለማችን ግዙፉ የኮንዶም አምራች በኢራን ጦርነት ምክንያት የዋጋ ጭማሪ ሊያደርግ ነው
የዓለማችን ግዙፉ የኮንዶም አምራች ኩባንያ ካሬክስ ኃላፊ በኢራን ጦርነት ምክንያት ለምርቶቹ የሚያስፈልጉ ጥሬ ዕቃዎች አቅርቦት ማስተጓጎሉን ከቀጠለ ኩባንያው ዋጋውን እስከ 30 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ እንደሚጨምር አስታወቁ።
የካሬክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጎህ ሚያህ ኪያት ለመገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት ግጭቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የምርት ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።
ማሌዥያ የሚገኘው ይህ ኩባንያ በዓመት ከአምስት ቢሊዮን በላይ ኮንዶሞችን ያመርታል።
ኩባንያው እንደ ዱሬክስ እና ትሮጃን ያሉ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ብራንዶች ከማምረት ባሻገር ለዩኬ ኤንኤችኤስ ዋነኛ የግብዓቶች አቅራቢ ነው።
ጎህ ይህንን የተናገሩት ከሮይተርስ እና ብሉምበርግ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሲሆን ቢቢሲ ኩባንያውን መረጃ ጠይቋል።
ቴህራን አሜሪካ እና እስራኤል ጦርነት ከከፈቱባት ጊዜ አንስቶ በሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ ላይ የሚንቀሳቀሱ መርከቦችን እንቅስቃሴ በማገዷ የዓለም የነዳጅ አቅርቦት ክፉኛ ተስተጓጉሏል።
ወሽመጡ ሙሉ በሙሉ በመዘጋቱ የተነሳ በዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለቶች ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል አስከትሏል።
ብዙውን ጊዜ የዓለም ድፍድፍ ዘይትና ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ (ኤልኤንጂ) ውስጥ አንድ አምስተኛ የሚሆነው እንዲሁም ሌሎች ፔትሮኬሚካሎች የሚያልፉት በባህረ ሰላጤው በኩል ነው።
ካሬክስ፣ ላቴክስን ጠብቆ ለማቆየት የሚያገለግለውን አሞኒያ፣ ሲሊኮን ያለባቸው ማለስለሻዎችን ለማምረት ከነዳጅ ዘይት የሚገኙ ምርቶችን ይጠቀማል።
ዘንድሮ የኮንዶም ፍላጎት በ30 በመቶ ገደማ ጭማሪ ያሳየ ቢሆንም የጭነት ወጪ በመጨመሩ እና የመርከብ ጉዞ መስተጓጎል እየተባባሰ በመምጣቱ እጥረት መፈጠሩን ጎህ ተናግረዋል።
"በአስቸጋሪ ጊዜያት ኮንዶም የመጠቀም አስፈላጊነት የሚጨምረው የወደፊት ሕይወትን፣ በሚቀጥለው ዓመት ሥራ ይኖርዎት እንደሆነ እርግጠኛ ስላልሆኑ ነው" ሲሉ ለብሉምበርግ ተናግረዋል።
"አሁን ልጅ ከወለዱ፣ ሌላ ተጨማሪ ሰው መመገብ ይኖርብዎታል" ሲል አክሏል።
የኮንዶም ዋጋ መጨመር የዓለምን የኢነርጂ ገበያዎች ያናወጠው የአሜሪካ እና የእስራኤል ጦርነት ለሸማቾች የሌሎች ሸቀጦችን ዋጋ እንዴት እያሳደገ እንዳለ ማሳያ ነው።
ጦርነቱ የአውሮፕላን ትኬት ዋጋ እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርጓል። ይህም ዝቅተኛው ዋጋ ያላቸው ትኬቶች ከአንድ ዓመት በፊት ከነበረው በአማካይ በ24 በመቶ የበለጠ ጭማሪ አስመዝግበዋል ሲል አንድ አዲስ ጥናት አመልክቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በባህረ ሰላጤው በኩል የሚደረጉ የጭነት መርከቦች ጉዞ መስተጓጎል የማዳበሪያ ዋጋ እንዲጨምር እና የኮምፒውተር ቺፖችን ለማምረት የሚያገለግል የሂሊየም እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
የታሸገ ውሃ አምራቾች ጥሬ እቃዎችን ለማግኘት ተቸግረው ጫና ውስጥ ገብተዋል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትራንስፖርት ዋጋ እየጨመረ በመምጣቱ የስኳር፣ የወተት እና የፍራፍሬ ዋጋ ሊጨምር እንደሚችል አስጠንቅቋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ድርድሩ እስኪቀጥል ድረስ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነት እንደሚራዘም ከተናገሩ በኋላ በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ስለሚደረገው የሰላም ድርድር በግልጽ የታወቀ ነገር የለም።