ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"ክፉኛ ስቅይት ደርሶብኛል፣ እጄንም አጥቻለሁ"- ትምህርትን ለመቀጠል የሚደረግ ትግል
ኦቭሪ ፍራይደይ ገና በ13 ዓመቱ በእንጀራ እናቱ 'ጠንቋይ ነው' ተብሎ በማዕከላዊ ናይጄሪያ ወደሚገኙ ባህላዊ ቤተ መቅደስ ተወስዷል። በዚህ ስፍራም ከባድ ስቅይት ተፈፅሞበታል።
ጎረቤቶች ለፖሊስ አሳውቀው ወደ ሆስፒታል ቢወሰድም ጉዳቱ በሕክምና የሚመለስ አልነበረም።
አሁን 19 ዓመቱ የሆነው ኦቭሪ "ዕፀዋት ቀማሚው ከሰል አመጣ፤ እጄ ላይ የሆነ ነገር አደረገ፤ እጄን ከእግሬ ጋር አብሮ አሰረ፤ በከሰሉ ውስጥ በርበሬ ጨመረ፤ ከዚያም በአንሶላ ሸፈነኝ" ሲል የተፈፀመበትን ስቃይ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ያስታውሳል።
ሐኪሞች ማደንዘዣ ሰጥተው ቀዶ ሕክምና እንዲያደርጉለት ተገደው ነበር። ኦቭሪ ሲነቃ የግራ እጁ ተቆርጦ አገኘው። የቀኝ እጁ ጣቶችም ተቆርጠው አሊያም ጠበሳ ይታይባቸው ነበር።
"አለቀስኩ፤ አለቀስኩ" ይላል ኦቭሪ ለቢቢሲ በቅፅበቱ የተሰማውን ሲገልፅ።
ከዚህ ቀጥሎ በመጡት ዓመታት ሰዎች በየመንገዱ ዓይናቸውን ያፈጡበታል ወይም ያፌዙበታል።
"ስወለድ ቢያውቁኝ ብዬ እመኛለሁ" ይላል።
ኦቭሪ ምንም እንኳ ሐዘኑ መራር ቢሆንም ሕይወቱን ለማስቀጠል ቁርጠኛ ነበር።
እንዲህም ሆኖ የናይጄሪያ ዩኒቨርስቲ የመግቢያ ፈተና ለመውሰድ ሲሞክር የትምህርት ሕይወቱ ለሁለት ዓመት ተስተጓጉሏል።
የፈተና ስርዓቱ ባዮሜትሪክስ በመሆኑ የአሻራ ሂደቱ እንደ እርሱ ዓይነቱን ሊያስተናግድ አልቻለም። ጠባሳ ካሉበት ጣቶቹ የጣት አሻራዎች መስጠት አልቻለም።
ለአሳዳጊው ምስጋና ይግባውና ከአካል ጉዳተኛ የመብት ተሟጋቾች ጋር የትምህርት ባለሥልጣናትን ማንነቱን ለማረጋገጥ የእግር ጣቶቹን አሻራ እንዲወሰድ በማድረጋቸው ዕድል ቀናው።
ኦቭሪ አሁን በናሳራዋ ዩኒቨርስቲ እንግሊዘኛ ቋንቋ እና ሥነ ፅሑፍ እያጠና ነው።
ከቤተሰቡ ዩኒቨርስቲ የገባ የመጀመሪያው ሰው ለመሆን በቅቷል።
"ሁሉም ሠው የሚታገልለት አያገኝም" ይላል፤ "አንዳንድ ሠዎች ተስፋ ቆርጠው መሞከራቸውን ያቆማሉ።"
ስካርሌት ኢዱኩ በናይጄሪያ ሰሜናዊ ግዛት ኮኖ ከተማ የራዲዮ ጋዜጠኛ ናት። እንደ ኦቭሪ ተመሳሳይ መሰናክል ገጥሟታል።
አብዛኞቹ ማንነትን የሚለዩ የማረጋገጫ መተግበሪያዎች ፊቷን ቃኝተው ለመለየት ይቸገራሉ። የ18 ወር ጨቅላ ሳለች የግራ ዓይኗን አጥታለች።
ይህ ተደጋጋሚ ራስ ምታት ሲሆን፤ ሲም ካርዷን ከ3ጂ ወደ 5ጂ ለማሳደግ የቴሌኮም ማዕከላት ሳትሄድ ባለችበት አካባቢ መቀየር አልቻለችም።
በምትኩ የቴሌኮም አቅራቢ ወደሆነው ድርጅት ዋና መስሪያ ቤት መጓዝ ነበረባት።
ከ35 ሚሊዮን የሚልቁ ናይጄሪያዊያን (ከአገሪቱ የሕዝብ ቁጥር 15 በመቶ) ከአካል ጉዳት ጋር እንደሚኖሩ ይገመታል።
እ.አ.አ በ2019 የናይጄሪያ ፓርላማ አካል ጉዳተኞች ላይ የሚደርስን መድልዎ የሚከለክል እና ሕዝባዊ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ዋስትና የሚሰጥ ወሳኝ ሕግ አፅድቋል።
ይህ ሕግ ለአካል ጉዳተኞች መብት የሚሟገት ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ኮሚሽን እንዲቋቋም ያደረገ ቢሆንም፤ "ከሞላ ጎደል የቀንድ አውጣ ፍጥነት" እንዳለው የኮሚሽኑ ዋና ፀሐፊ አዩባ ቡርኪ-ጉፏን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ ዋና ፀሐፊው ተስፈኛ ናቸው፤ "የሺህ ኪሎ ሜትሮች ጉዞ በአንድ እርምጃ ነው የሚጀምረው" ይላሉ።
ከሕጉ መፅደቅ በኋላ የአገሪቱ የፌደራል ፈተናዎች መመዘኛ ለአካል ጉዳተኞች የፈተና ክፍያን በማስቀረት የተለያዩ ፍላጎቶች ላሏቸው ተማሪዎች የሚሰራ ማዕከል ማቋቋሙን በአዎንታዊ ጎን አንስተዋል።
ላፊያ የተባለው የፌደራል ዩኒቨርስቲ የአካል ጉዳት ላለባቸው ተማሪዎች 75 በመቶ ክፍያዎችን አንስቷል።
"በድንገት ዩኒቨርሰቲዎች ቅበላቸው በከፍተኛ ሁኔታ ጨመረ" የሚሉት ፀሐፊው፤ "ምክንያቱም አካል ጉዳት ያለባቸው ሁሉም ሠዎች ከጥቅሙ ተቋዳሽ መሆን በመፈለጋቸው ነው" ይላሉ።
በሌጎስ የልዩ ፍላጎት መምህር የሆኑት ቹኬሜካ ችምዲብሪ እንደሚሉት ናይጄሪያ የአካል ጉተኞችን ፍላጎት ለማሟላት ጥረቷን አሳድጋለች።
"አካታችነት ውለታ አይደለም። ኃላፊነት ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ተደራሽነት የሕንፃ መወጣጫ ከመገንባት ያለፈ እንደሆነም ያብራራሉ።
ተደራሽነት በትምህርት ክፍሎች የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዎች፣ ማየት ለተሳናቸው ተማሪዎች የመማሪያ ቁሶች፣ የሰለጠኑ መምህራን እና የተለያዩ ተጠቃሚዎችን ከግምት ውስጥ አስገብተው የተነደፉ የዲጂታል መድረኮች ማለት ነው።
"አብዛኞቹ አካል ጉዳተኞች በጉዳታቸው ብቻ የተገደቡ አይደሉም። እነሱን ከግምት ውስጥ ሳያስገባ በተነደፈ ስርዓት የተገደቡ ናቸው" ይላሉ።
የ48 ዓመቷ አቢዮስ ፋላዴ በደቡብ ምዕራብ ከተማዋ ኢባዳን ፀሐፊ ናት። ዊልቸር ተጠቃሚ የሆነችው አቢዮስ አካል ጉዳተኝነት "የሕይወት ሽክርክሪት አካል ነው" ትላለች።
"ገና በልጅነት ሊደርስብን ይችላል፤ በኋላም ላይ ሊደርስብን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የዘላለም ሊሆን ይችላል፤ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ጊዜያዊ። ነገር ግን አካል ጉዳተኝነት እግዚአብሔር የተለያዩ አድርጎ እንዴት እንደፈጠረን ማሳያ ነው።"
አቢዮስ በ10 ዓመቷ ትምህርት ቤት እስክትሄድ ስረስ ራሷን ከሌላው ሠው የተለየች አድርጋ አታይም ነበር።
"ከዓለም እና ከውስብስብ ነገሮች ጋር ተዋወቅኩ" ትላለች። "የአካል ጉዳት ያለበት ሠው የምንፈልገው ዓለም አካል አልነበሩም።"
ዛሬም ድረስ እንዲህ ዓይነት ስሜት አላት። "መሄድ የምችልባቸው ቦታዎች እና መሄድ የማልችልባቸው ቦታዎች ዝርዝር አለ።"
"መውጣት ስፈልግ ሠው ይዤ እውጣለሁ። ምክንያቱም ሠዎች ስያፈጡብኝ፤ ሲጠቋቆሙ እንዳላስተውል። ብቸኛ ሆኖ ከመጋፈት ይልቅ ይቀላል።"
ከባቢው ደግሞ ችግሩን ያባብሰዋል።
በበርካታ የናይጄሪያ ከተሞች መንገዶች የተመቻቹ አሊያም በሰፊ ክፈተቶች የተቋረጡ፣ ለጥገና በሚል ክፍት የውሃ ቦዮች ስለሚገኙ ለመንቀሳቀስ ከባድ ወይም የማይቻል ነው።
በገጠራማ አካባቢዎች እግረኛ መንገዶች አለመኖር የዊልቸር ተጠቃሚዎች ብዙውን ጊዜ ባልተስተካከሉ መንገዶች ወይም አደገኛ በሆኑ መንገዶች ላይ መንቀሳቀስ የግድ ይላቸዋል።
የሕዝባዊ ሕንፃዎች መወጣጫዎች እና የዊልቸር ተጠቃሚዎች ያለ እርዳታ ወደ ባንኮች፣ ሆስፒታሎች ወይም የመንግሥት ቢሮዎች ለመግባት እምብዛም አይመቹም።
ሁኔታውን የሚያባብሰው ናይጄሪያ እያንዳንዱን የዊልቸር፣ የመስሚያ መርጃ መሣሪያ እና የመንቀሳቀሻ መሣሪያ ከውጭ ማስገባት አለባት።
"ከአስር የአካል ጉዳተኞች ዘጠኙ የተወሰነ አይነት አጋዥ መሣሪያ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፤ እናም አንዳቸውም በአገር ውስጥ የተመረቱ ካልሆኑ ትልቅ ፈተና ይሆናል" ይላሉ የኮሚሽኑ ዋና ፀሐፊ።
ተሟጋቾች አንድ በመቶ የሚሆነው በጀት በእያንዳንዱ የመንግሥት ደረጃ ላሉ አካል ጉዳተኞች እንዲመደብ ጥሪ እያቀረቡ ነው።
አካታች መሠረተ ልማቶች እና አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ማስፋፋት ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ይጠይቃል። ምንም እንኳን ተሟጋቾች ጠንካራ ቁርጠኝነት እና ነባር ሕጎችን ማስፈጸም እንደ በጀት መመደብ ወሳኝ ናቸው።